ምዕራፍ 1

1፤ በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፥ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ።

2፤ ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት

3፤ ከወሩም በአምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በከለዳውያን አገር በኮቦር ወንዝ ወደ ቡዝ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፥

4፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም እሳት መጣ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፥ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ እንደሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ ነበረ።

5፤ ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር።

6፤ ለእያዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት።

7፤ እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፤ የእግራቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፤ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር።

8፤ በክንፎቻቸውም በታች በእያራቱ ጐድናቸው እንደ ሰው እጅ ነበረ፤ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው።

9፤ ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ የተያያዘ ነበረ፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር፥ እያንዳንዱም ፊቱን አቅንቶ ይሄድ ነበር።

10፤ የፊታቸው አምሳያ እንደ ሰው ፊት ነበረ፥ ለአራቱም በስተ ቀኛቸው እንደ አንበሳ ፊት፥ በስተ ግራቸውም እንደ ላም ፊት ነበራቸው፥ ለአራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው።

11፤ ክንፋቸውም በላይ ተዘርግቶ ነበር፥ የእያንዳንዱም ሁለት ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፥ ሁለት ሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር።

12፤ እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።

13፤ በእንስሶቹ መካከል እንደሚነድድ የእሳት ፍም ያለ ምስያ ነበረ፤ በእንስሶች መካከል ወዲህና ወዲያ የሚሄድ እንደ ፋና ያለ ምስያ ነበረ፤ ለእሳቱም ፀዳል ነበረው፥ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር።

14፤ እንስሶቹም እንደ መብረቅ ምስያ ይሮጡና ይመለሱ ነበር።

15፤ እንስሶችንም ስመለከት፥ እነሆ፥ በአራቱ እንስሶች አጠገብ በምድር ላይ አንድ አንድ መንኰራኵር አየሁ።

16፤ የመንኰራኵሩም መልክ እንደ ቢረሌ ነበረ፤ አራቱም አንድ አምሳያ ነበሩ፤ ሥራቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ።

17፤ በእያራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።

18፤ ቁመታቸውም የረዘመና የሚያስፈራ ነበረ፤ የአራቱም ክበብ ዙሪያው በዓይን ተሞልቶ ነበር።

19፤ እንስሶቹም በሄዱ ጊዜ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ሄዱ። እንስሶቹም ከምድር ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ መንኰራኵሮቹ ከፍ ከፍ አሉ።

20፤ መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱ ሄዱ፤ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና መንኰራኵሮቹ በእነርሱ አጠገብ ከፍ ከፍ አሉ።

21፤ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና እነዚያ ሲሄዱ እነዚህ ይሄዱ ነበር፤ እነዚያም ሲቆሙ እነዚህ ይቆሙ ነበር፤ እነዚያም ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር።

22፤ ከእንስሶች ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር።

23፤ ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት።

24፤ ሲሄዱም የክንፎቻቸው ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ፥ እንደ ሁሉን የሚችል የአምላክም ድምፅ፥ እንደ ታላቅም ሠራዊት ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

25፤ በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

26፤ በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ።

27፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ።

28፤ በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።

ምዕራፍ 2

1፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእግርህ ቁም እኔም እናገርሃለሁ አለኝ።

2፤ በተናገረኝም ጊዜ መንፈስ ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ የሚናገረኝንም ሰማሁ።

3፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእኔ ላይ ወደ ዐመፁ ወደ ዓመፀኞች ሰዎች ወደ እስራኤል ልጆች እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፁብኝ።

4፤ እነርሱ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸውም የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው።

5፤ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ነቢይ በመካከላቸው እንዳለ ያውቃሉ።

6፤ አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ኵርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም፥ አትፍራቸው፥ ቃላቸውንም አትፍራ፤ አንተ ቃላቸውን አትፍራ፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።

7፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ቃሌን ትነግራቸዋለህ።

8፤ አንተ ግን፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ስማ፤ እንደዚያ እንደ ዓመፀኛው ቤት ዓመፀኛ አትሁን፤ አፍህን ክፈት የምሰጥህንም ብላ።

9፤ ባየሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ እጅ ወደ እኔ ተዘርግታ ነበር፤ እነሆም፥ የመጽሐፍ ጥቅልል ነበረባት።

10፤ በፊቴም ዘረጋው፥ በውስጥና በውጭም ተጽፎበት ነበር፤ ልቅሶና ኀዘን ዋይታም ተጽፎበት ነበር።

ምዕራፍ 3

1፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር አለኝ።

2፤ አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ።

3፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ።

4፤ እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ተናገራቸው።

5፤ ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህምና፤

6፤ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ቃላቸውንም ታውቅ ዘንድ ወደማይቻልህ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነዚያስ ልኬህ ቢሆን ኖሮ በሰሙህ ነበር።

7፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና፥ እኔንም መስማት እንቢ ብለዋልና የእስራኤል ቤት አንተን አይሰሙም።

8፤ እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ።

9፤ ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንዳለ አልማዝ ግምባርህን አጠንክሬአለሁ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑ አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ።

10፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ የነገርሁህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ተቀበል በጆሮህም ስማ።

11፤ ተነሥተህም ወደ ተማረኩ ወደ ወገንህ ልጆች ሂድ፤ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው አለኝ።

12፤ መንፈስም አነሣኝ፥ በኋላዬም። የእግዚአብሔር ክብር ከቦታው ይባረክ የሚል የጽኑ ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ።

13፤ የአራቱም እንስሳ ክንፎች እርስ በርሳቸው ሲማቱ፥ በአጠገባቸውም የመንኰራኵሮችን ድምፅ፥ የጽኑውንም ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ።

14፤ መንፈስ አንሥቶ አስወገደኝ፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ሙቀት ሄድሁ፥ የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ በርትታ ነበር።

15፤ በቴልአቢብም ወዳሉ በኮቦርም ወንዝ አጠገብ ወደ ተቀመጡ ምርኮኞች መጣሁ፥ በተቀመጡበትም ቦታ ተቀመጥሁ፤ በዚያም ሰባት ቀን በድንጋጤ በመካከላቸው ተቀመጥሁ።

16፤ ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

17፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የአፌን ቃል ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው።

18፤ እኔ ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።

19፤ ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቅ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።

20፤ ደግሞ ጻድቁ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአት በሠራ ጊዜ እኔ በፊቱም ዕንቅፋትን ሳደርግ፥ እርሱ ይሞታል፤ አንተም አላስጠነቀቅኸውምና በኃጢአቱ ይሞታል ያደረጋትም ጽድቅ ነገር አትታሰብለትም፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።

21፤ ነገር ግን ኃጢአት እንዳይሠራ ጻድቁን ብታስጠነቅቅ እርሱም ኃጢአት ባይሠራ፥ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን አድነሃል።

22፤ በዚያም የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ እርሱም። ተነሥተህ ወደ ቈላው ሂድ በዚያም እናገርሃለሁ አለኝ።

23፤ እኔም ተነሥቼ ወደ ቈላው ሄድሁ፤ እነሆም፥ በኮቦር ወንዝ እንዳየሁት ክብር ያለ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፥ በግምባሬም ተደፋሁ።

24፤ መንፈስም ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ። ሂድ፥ ገብተህ ቤትህን ዝጋ።

25፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ ገመድ ያደርጉብሃል ያስሩህማል፥ አንተም በመካከላቸው አትወጣም፤

26፤ እኔም ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና የሚዘልፍ ሰው አትሆንባቸውም።

27፤ ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አንተ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ ትላቸዋለህ።

ምዕራፍ 4

1፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጡብን ወስደህ በፊትህ አኑራት የኢየሩሳሌምንም ከተማ ስዕል ሳልባት ክበባት፥

2፤ ምሽግም ሥራባት፥ አፈርም ደልድልባት፥ ሰፈርም አቁምባት፥ በዙሪያዋም የሚያፈርስ ግንድ አድርግባት።

3፤ የብረት ምጣድም ወስደህ በአንተና በከተማይቱ መካከል ለብረት ቅጥር አድርገው፥ ፊትህንም ወደ እርስዋ አቅና፥ የተከበበችም ትሆናለች አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።

4፤ አንተም በግራ ጐድንህ ተኛ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት አኑርባት፤ በምትተኛበትም ቀን ቍጥር ኃጢአታቸውን ትሸከማለህ።

5፤ እኔም የኃጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀን ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፤ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ።

6፤ እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ በቀኝ ጐድንህ ትተኛለህ፥ የይሁዳንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፤ አንድን ዓመት አንድ ቀን አድርጌ አርባ ቀን ሰጥቼሃለሁ።

7፤ ክንድህን ዕራቁቱን አድርገህ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ክቡ ታቀናለህ፥ ትንቢትም ትናገርባታለህ።

8፤ እነሆም፥ ገመድ አደርግብሃለሁ፥ የምትከበብበትንም ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከጐድን ጐድንህ አትገላበጥም።

9፤ አንተም ስንዴንና ገብስን ባቄላንና ምስርን ጤፍንና አጃን ወደ አንተ ውሰድ፥ በአንድ ዕቃም ውስጥ አድርገህ እንጀራ ጋግር፤ በጐድንህ እንደ ተኛህበት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ትበላዋለህ።

10፤ የምትበላውም በሚዛን በየቀኑ ሀያ ሀያ ሰቅል ይሁን፥ በየጊዜው ትበላዋለህ።

11፤ ውኃውንም በልክ የኢን መስፈሪያ ከስድስት እጅ አንድን እጅ ትጠጣለህ፥ በየጊዜው ትጠጣዋለህ።

12፤ እንደ ገብስ እንጐቻም አድርገህ ትበላዋለህ፥ ከሰውም በሚወጣ ፋንድያ በፊታቸው ትጋግረዋለሁ።

13፤ እግዚአብሔርም። እንዲሁ የእስራኤል ልጆች እነርሱን በምበትንባቸው በአሕዛብ መካከል ርኩስ እንጀራቸውን ይበላሉ አለ።

14፤ እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነሆ፥ ሰውነቴ አልረከሰችም፤ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጥንብና አውሬ የሰበረውን ከቶ አልበላሁም፥ ርኩስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም አልሁ።

15፤ እርሱም። እነሆ፥ በሰው ፋንድያ ፋንታ ኩበት ሰጥቼሃለሁ በእርሱም እንጀራህን ትጋግራለህ አለኝ።

16፤ ደግሞም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ የኢየሩሳሌምን እንጀራ በትር እሰብራለሁ፥ እየፈሩም እንጀራን በሚዛን ይበላሉ፥ እየደነገጡም ውኃን በልክ ይጠጣሉ፤

17፤ ይህም እንጀራንና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲደነቁ፥ በኃጢአታቸውም እንዲሰለስሉ ነው።

ምዕራፍ 5

1፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የተሳለን ጐራዴ ውሰድ፥ እንደ ጢም መላጫ ወደ አንተ ትወስደዋለህ፥ ራስህንና ጢምህንም ትላጭበታለህ፤ ሚዛንንም ውሰድ ጠጕሩንም ትከፋፍላለህ።

2፤ የመከበብም ወራት በተፈጸመ ጊዜ በከተማይቱ መካከል ሢሶውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ሢሶውንም ወስደህ ዙሪያውን በጐራዴ ትመታለህ፥ ሢሶውንም ወደ ነፋስ ትበትናለህ እኔም በኋላቸው ጐራዴ እመዝዛለሁ።

3፤ ከዚያም በጥቂቱ ውሰድ በመጐናጸፊያህም ጫፍ ቋጥራቸው።

4፤ ከእነርሱም ደግሞ ወስደህ በእሳት ውስጥ ትጥላለህ በእሳትም ታቃጥላቸዋለህ፤ ከዚያም በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ እሳት ትወጣለች።

5፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህች ኢየሩሳሌም ናት፤ በአሕዛብም መካከል አድርጌአታለሁ፥ አገሮችም በዙሪያዋ አሉ።

6፤ እርስዋም ከአሕዛብ ይልቅ ፍርዴን በኃጢአት ለወጠች በዙሪያዋም ካሉ አገሮች ሁሉ ይልቅ ትእዛዜን ተላለፈች፤ ፍርዴን ጥለዋልና፥ በትእዛዜም አልሄዱምና።

7፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዙሪያችሁ ላሉት አሕዛብ ሰበብ ሆናችኋልና፥ በትእዛዜም አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አልጠበቃችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንዳሉ እንደ አሕዛብ ፍርድ እንኳ አላደረጋችሁምና

8፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ነኝ፥ አሕዛብም እያዩ ፍርድን በመካከልሽ አደርጋለሁ።

9፤ ስለ ርኵሰትሽም ሁሉ ያልሠራሁትን እርሱንም የሚመስል ደግሞ የማልሠራውን ነገር እሠራብሻለሁ።

10፤ ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አደርግብሻለሁ ከአንቺም የቀረውን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ።

11፤ ስለዚህ፥ እኔ ሕያው ነኝና በእድፍሽና በርኵሰትሽ መቅደሴን ስላረከስሽ፥ ስለዚህ በእውነት እኔ አሳንስሻለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም።

12፤ ከአንቺም ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፥ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሢሶውም በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃል፤ ሢሶውንም ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።

13፤ ቍጣዬም ይፈጸማል መዓቴንም እጨርሳለሁ እጽናናማለሁ፥ መዓቴንም በፈጸምሁባቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር በቅንዓቴ እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ።

14፤ በዙሪያሽም ባሉ በአሕዛብ መካከል በሚያልፉም ሁሉ ፊት ባድማና መሰደቢያ አደርግሻለሁ።

15፤ በቍጣና በመዓት፥ በመዓትም ዘለፋ ፍርድን ባደረግሁብሽ ጊዜ በዙሪያሽ ላሉ አሕዛብ መሰደቢያና መተረቻ፥ ተግሣጽና መደነቂያ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

16፤ ለማጥፋትም የሆነውን፥ አጠፋችሁም ዘንድ የምሰድደውን የራብ ፍላጻ በላያችሁ በሰደድሁ ጊዜ፥ ራብን እጨምርባችኋለሁ፥ የእንጀራችሁንም በትር እሰብራለሁ።

17፤ ራብንና ክፉዎችን አራዊት እሰድድባችኋለሁ፥ ልጆቻችሁንም ያጠፋሉ፤ ቸነፈርና ደምም በአንቺ ዘንድ ያልፋሉ፤ ሰይፍንም አመጣብሻለሁ። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

ምዕራፍ 6

1፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

2፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አቅና ትንቢትም ተናገርባቸው።

3፤ እንዲህም በል። የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች ለምንጮችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል። እኔ፥ እነሆ፥ እኔ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ የኮረብታው መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ።

4፤ መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይሰበራሉ፤ ተወግተውም የሞቱትን ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ።

5፤ የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች በጣዖቶቻቸው ፊት አኖራለሁ፥ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ።

6፤ በምትኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ከተሞቹ ይፈርሳሉ፥ የኮረብታው መስገጃዎችም ሁሉ ውድማ ይሆናሉ፥ መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ ባድማም ይሆናሉ፥ ጣዖቶቻችሁም ይሰበራሉ ያልቃሉም፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይቈረጣሉ፥ ሥራችሁም ይሻራል።

7፤ ተወግተውም የሞቱት በመካከላችሁ ይወድቃሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

8፤ ነገር ግን በአገሮች በተበተናችሁ ጊዜ ከሰይፍ ያመለጡትን ቅሬታ በአሕዛብ መካከል አስቀርላችኋለሁ።

9፤ ከእናንተም የዳኑት ከእኔ በራቀው በአመንዝራ ልባቸውና ጣዖቶቻቸውን በተከተሉ በአመንዝራ ዓይኖቻቸው የተሰበርሁትን እኔን ወደ እነርሱ በተማረኩት አሕዛብ መካከል ሆነው ያስቡኛል፤ በርኵሰታቸውም ሁሉ ስላደረጉት ክፋት ራሳቸውን ይጸየፋሉ።

10፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይህን ክፉ ነገር አደርግባቸው ዘንድ መናገሬ በከንቱ አይደለም።

11፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእጅህ አጨብጭብ በእግርህም አሸብሽብ እንዲህም በል። በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይወድቃሉና ስለ እስራኤል ቤት ስለ አስጸያፊ ሥራዎቻቸው ሁሉ ወዮ!

12፤ በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፥ በቅርብም ያለው በሰይፍ ይወድቃል፥ የቀረውና የዳነውም በራብ ይሞታል፤ እንዲሁ መዓቴን እፈጽምባቸዋለሁ።

13፤ ተወግተውም የሞቱ ሰዎቻቸው በጣዖቶቻቸው መካከልና በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ፥ ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ባቀረቡበት ስፍራ፥ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ በተራሮችም ራስ ሁሉ ላይ፥ ከለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ቅጠሉም ከበዛ ከአድባር ዛፍ ሁሉ በታች በሆኑ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

14፤ እጄንም እዘረጋባቸዋለሁ፥ በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምድሪቱን ከዴብላታ ምድረ በዳ ይልቅ ውድማና በረሃ አደርጋታለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ምዕራፍ 7

1፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

2፤ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል። ፍጻሜ፥ በምድሪቱ በአራቱ ማዕዘን ላይ ፍጻሜ ደርሶአል።

3፤ አሁን ፍጻሜ በአንቺ ላይ ነው፥ ቍጣዬንም እሰድድብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ።

4፤ ዓይኔም አይራራልሽም እኔም አላዝንም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

5፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ክፉ ነገር፥ አንድ ክፉ ነገር፥ እነሆ፥ ይመጣል።

6፤ ፍጻሜ መጥቶአል፥ ፍጻሜ መጥቶአል፥ ነቅቶብሻል፤ እነሆ፥ ደርሶአል።

7፤ በምድር የምትቀመጥ ሆይ፥ ተራህ ደርሶአል፥ ጊዜ መጥቶአል፥ ቀን ቀርቦአል፤ የሽብር ቀን ነው እንጂ በተራራ ላይ ያለ እልልታ አይደለም።

8፤ አሁን በቅርብ መዓቴን አፈስስብሻለሁ፥ ቍጣዬንም እፈጽምብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ።

9፤ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም፤ እንደ መንገድሽም መጠን አመጣብሻለሁ፥ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር የምቀሥፍ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

10፤ እነሆ ቀኑ፥ እነሆ፥ መጥቶአል፤ ተራህ ወጥቶአል፤ ብትር አብቦአል፥ ትዕቢትም አጅብጅፎአል።

11፤ ግፍ ወደ ክፋት ብትር ተነስቶአል፤ ከእነርሱና ከብዛታቸው ከሀብታቸውም ምንም አይቀርም፥ የሚያለቅስላቸውም የለም።

12፤ ጊዜው መጥቶአል፥ ቀኑ ቀርቦአል፤ መዓት በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና የሚገዛ ደስ አይበለው የሚሸጥም አያልቅስ።

13፤ የሚሸጥ ወደሸጠው ነገር አይመለስም፥ ሰውም በነፍሱ ኃጢአት አይጸናም።

14፤ መለከቱን ነፍተዋል ሁሉንም አዘጋጅተዋል፤ ነገር ግን መዓቴ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና ወደ ሰልፍ የሚሄድ የለም።

15፤ ሰይፍ በውጭ ቸነፈርና ራብ በውስጥ አለ፤ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፥ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይፈጁታል።

16፤ ከእነርሱም የሚሸሹ ይድናሉ በተራራም ላይ ይሆናሉ፤ እኔም በኃጢአታቸው ሁሉን እገድላለሁ።

17፤ እጅ ሁሉ ትደክማለች ጕልበትም ሁሉ እንደ ውኃ ትቀልጣለች።

18፤ ማቅም ይለብሳሉ ድንጋጤም ይሸፍናቸዋል፤ በፊትም ሁሉ ላይ እፈረት ይሆናል፥ ራሳቸውንም ሁሉ ይነጩታል።

19፤ ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጕድፍ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም። እርሱ የኃጢአታቸው ዕንቅፋት ሆኖአልና ሰውነታቸውን አያጠግቡም ሆዳቸውንም አይሞሉም።

20፤ የክብሩንም ጌጥ ወደ ትዕቢት ለወጡ፥ የርኵስነታቸውንም ምስሎች አደረጉባት፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ አድርጌአታለሁ።

21፤ በባዕድም እጅ ለንጥቂያ፥ በምድር ኃጢአተኞችም እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እነርሱም ያረክሱአታል።

22፤ ፊቴን ከእነርሱ ዘንድ እመልሳለሁ፥ ምሥጢሬንም ያረክሳሉ፤ ወንበዴዎችም ይገቡባታል ያረክሱአትማል።

23፤ ምድር ደም ባመጣው በደል፥ ከተማም በግፍ ተሞልታለችና ሰንሰለት ሥራ።

24፤ ከአሕዛብ ዘንድ ከሁሉ የሚከፉትን አመጣለሁ ቤቶቻቸውንም ይወርሳሉ፤ የኃያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፥ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ።

25፤ ጥፋት መጥቶአል፤ ሰላምም ይሻሉ እርሱም አይገኝም።

26፤ ድንጋጤ በድንጋጤ ላይ ይመጣል፥ ወሬም ወሬውን ይከተላል፥ ከነቢዩም ዘንድ ራዕይን ይሻሉ፤ ከካህኑም ዘንድ ትምህርት፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ ምክር ይጠፋል።

27፤ ንጉሡም ያለቅሳል፥ አለቃም ውርደትን ይለብሳል፥ የምድርም ሕዝብ እጅ ትንቀጠቀጣለች፤ እንደ መንገዳቸውም መጠን አደርግባቸዋለሁ፥ በፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።